AMN – ሰኔ 22/2018 ዓ.ም
“ኢትዮጵያና ሶማሊያ ከድንበር በላይ የሚጋሩት እጅግ ውድ የሆነውን ሕዝባቸውን እና የጋራ እጣ ፈንታቸውን ነው።” ይህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተገለጸው መልዕክት የሁለቱን ጎረቤት አገራት ታሪካዊና የማይነጣጠል ትስስር ያሳያል።
የኢትዮጵያና የሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጎረቤትነት፣ በባህልና በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ላይ የተመሰረተ ረጅም ታሪክ ያለው ቢሆንም በርካታ ውጣ ውረዶችን ማስተናገዱ ይታወቃል።
ሆኖም አሁን ላይ በአገራቱ መሪዎች ዲፕሎማሲያዊ ጥበብና ቀጣይነት ባላቸው ውይይቶች አማካኝነት፣ ግንኙነቱ ወደ አስተማማኝ መረጋጋትና ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡
የሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ቁልፍ መሆኑን የምታምነው ኢትዮጵያ፤ አል ሸባብ የሽብር ቡድንን ለመዋጋት በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ ስር ሠራዊቷን በማሰማራት የሶማሊያን መንግሥትና ሕዝብ ስትደግፍ ቆይታለች።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ለሶማሊያ ሰላም የከፈሉትን መስዋዕትነት የሶማሊያ መንግስትና ሕዝብ ሁልጊዜም እንደማይዘነጋው በተለያዩ ጊዜያት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ይህ የወታደራዊና የደኅንነት ትብብር የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ አዎንታዊ አቅጣጫ ለመምራት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
በተለይም የኢትዮጵያና የሶማሊያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከአንካራው ውይይት በኋላ ይበልጥ ወደ ተጨባጭ የትብብር ምዕራፍ መሸጋገሩን ወቅታዊ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች ያሳያሉ፡፡
በቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶዋን አስተናጋጅነት በተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ አንዳቸው የሌላውን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት በማክበር፣ በቀጠናዊ የኢኮኖሚና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ይህ ስምምነት ለሀገራቱ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝቶችና ለሁለትዮሽ ግንኙነቱ መሻሻል ጠንካራ መሠረት ጥሏል። ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት የዲፕሎማሲ ማዕከል ወደ ሆነችው አዲስ አበባ መግባታቸው ነው።
ጉብኝታቸውን ተከትሎም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ጋር በኢኮኖሚያዊ ትስስር፣ ደኅንነት እና በቀጠናዊ መረጋጋት ዙሪያ በመተማመንና በመከባበር ላይ የተመሠረተ የሁለትዮሽ ውይይት ማካሄዳቸውን አስታውቀዋል።
አገራቱ ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት እየተደረጉ ያሉ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ውይይቶች ያመላታክታሉ፡፡
ከጥቂት ወራት በፊትም ሁለቱ መሪዎች ከጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ዑመር ጌሌ ጋር በጅቡቲ ያካሄዱት የሦስትዮሽ ጉባኤ በቀጠናው የጋራ ተጠቃሚነትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የተጀመረው ስኬታማ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አካል መሆኑ የሚታወስ ነው።
በትዝታ መንግስቱ