AMN- ግንቦት 7/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ የመፅናትና የማሸነፍ፣ የድላችንን አሻራ፣ የከተማችንን ለውጥ የታዘቡ የውጭ ሀገራት ፀሀፊዎችና ባህር ማዶ የሚኖሩ ምሁራን በራሳቸው ተነሳሽነትና ገንዘብ ያሳተሙትን “THE REMAKING OF ADDIS ABABA/አዲስ አበባን እንደ አዲስ ” የተሰኘ መጽሐፍ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት አስመርቀናል ብለዋል።

ይህ መጽሀፍ ለህዝባችን ቃል ገብተን፣ ቃላችንን በተግበር የቀየርንበትን ታሪክ የሚተርክ ነው። ሕዝባችን በገንዘቡ፣ በጉልበቱ፣ በሀሳቡ የተሳተፈበት የሁላችንም ውጤት ነው፡፡
ከባህር ማዶ እንግሊዛዊው ጸሐፊ ኘሮፌሰር ስሞን ሊ፣ ዶ/ር ክሌመንት ካቱሉሺ፣ ትዉልደ ኢትዮዽያዊው ዶ/ ር ሂርዾ ቁምቢ እና ቡድናቸው በጋራ የጻፋት መጽሐፍ፣ ጠንካራ እሳቤ ወደ ተጨባጭ ስኬት መቀየሩን እና የአዲስ አበባን ትራንስፎርሜሽን ያሳየ እንዲሁም ለትውልድ የሚሻገር ታሪክን የሰነደ በመሆኑ ለጸሀፊዎቹ ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል።

የባህር ማዶ ሰዎችን ቀልብ በሳበው የከተማችን ልማት፤ የሺዎች ድካምና ብርታት፣ የትወልድ አሻራ ለማሳረፍ የደከሙትን ሁሉ እውቅና እንሰጣለን፤ እናመሰግናለን!!!
የለውጥ ጉዞው የሁላችንም ኩራት ሲሆን፣ በቀጣይም ከተማችንን ይበልጥ ለማበልጸግ የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።