የአዲስ አበባ እህት ከተሞች፡- ከናይሮቢ እስከ ባኩ

You are currently viewing የአዲስ አበባ እህት ከተሞች፡- ከናይሮቢ እስከ ባኩ

በአዲስ አበባ እና በባኩ መካከል የተደረገው የእህትማማችነት ከተማ ስምምነት አዲስ አበባ ለተያያዘችው የልማት ስራ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ተመላክቷል

የብሪታንያ የታሪክ ጸሐፊ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ኦቨርይ ስለ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት፣ ስለ ናዚ ጀርመን፣ ስለ ወታደራዊ ታሪክ እና በጦርነቱ ወቅት የወደሙ የአውሮፓ ከተሞችን አስመልክቶ ባደረጓቸው ጥናቶች ይታወቃሉ፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ ጥር 1 ቀን 2013 “The bombing war: Europe From 1939 To 1945” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፋቸው እንደ ሃምቡርግ፣ ድሬስደን፣ በርሊን፣ ዋርሶ፣ ሮተርዳም እና ለንደን ያሉ ታላላቅ ከተሞች ላይ የደረሰውን ጉዳት ያብራራሉ።

በከተሞች ላይ የሚደርሰውን እንዲህ አይነቱን ጉዳት ለማካካስም ሆነ ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ የእህትማማች ከተሞች ግንኙነት መመስረት አስፈላጊ ነው፤ የእህትማማች ከተሞች ግንኙነት መመስረት የጀመረው ከዚሁ አስከፊ ጦርነት በኋላ መሆኑንም ታሪክ ይነግረናል፡፡ በተለይም በግጭቱ በተጎዱ ሀገራት መካከል እርቅ ለመፍጠር እና ሰላምን እንደገና ለመገንባት የእህትማማች ከተሞች ግንኙነትን በመመስረት የሰላምና የዕድገት መንገዶችን ቀይሰዋል፡፡

እስከዛሬም ከ20 እስከ 30 ሺህ የሚደርሱ የዓለማችን ከተሞች የእህትማማችነት ስምምነትን በመመስረት ችግሮቻቸውን የሚፈቱበትን እና እድገቶቻቸውንም የሚያስቀጥሉባቸውን የጋራ ብልሃቶች በመዘየድ በንቃት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ድዋይት ዲ. አይዘንሃወር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ “የዜጎች ዲፕሎማሲ”ን ከፍ ለማድረግ በሚል እ.ኤ.አ 1956 የመሰረቱት ‘ሲስተር ሲቲስ ኢንተርናሽናል’ የተሰኘው ድርጅት ይፋ ያደረጋቸው የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አዲስ አበባም የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን ቤጂንግ፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ኪጋሊ እና አሁን ባኩን ጨምሮ ከበርካታ ከተሞች ጋር የእህትማማች ግንኙነትን መስርታለች፡፡ የመጀመሪያዋ አዲስ አበባ እህት ከተማ ናይሮቢ ስትሆን ስምምነቱም የተፈፀመው እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ነበር። በአሁኑ ወቅት ከተማዋ ከ30 በላይ የዓለማችን ከተሞች ጋር የእህትማማችነት ስምምነቶችን አድርጋለች፡፡

ከእነዚህም ውስጥ የደቡብ ኮሪያ ቹንቼዮን፣ የእስራኤል ቤርሳቤህ፣ የሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ፣ የደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ፣ የሱዳን ካርቱም፣ የዛምቢያ ሉሳካ፣ የቻይና ቤጂንግ እና ቾንግኪንግ፣ የፈረንሳይ ግራንድ ሊዮን፣ የጀርመን ላይፕዚግ፣ የቱርክ አንካራ፣ ዋሽንግተን ዲሲ እና ከአሜሪካ ሎስ አንጀለስ ይገኙበታል።

ለአብነት ከቻይና ከተሞች ቤጂንግ እና ቾንግቺንግ ጋር የተደረገው ስምምነትም በዘመናዊ የከተማ መሪ ዕቅድ፣ በትራንስፖርት አስተዳደር እና በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ዙሪያ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የስልጠና እድሎችን አስገኝቶላታል፡፡ የቱርክዬ አንካራ ከተማም በአስተዳደር ሰራተኞች አቅም ግንባታ ላይ ስትሰራ፣ ሌይፕዚግ ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በምርምርና በትምህርት ዘርፉ ላይ የበኩሏን ትብብር ታደርጋለች፡፡

እንደ ኢስታንቡል ካሉ ከተሞች ጋር የተደረጉ ስምምነቶችም ለቱርክዬ ባለሀብቶች መምጣት ትልቅ በር በመክፈት በሀገራችን የጨርቃ ጨርቅ እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

እንደ ቤጂንግ፣ ሼንዘን እና ሻንጋይ ያሉ የቻይና ከተሞች ደግሞ ለአዲስ አበባ የኢንዱስትሪ ዞኖች መስፋፋትና ለታላላቅ መሰረተ ልማቶች እንደ ቀላል ባቡር የፋይናንስ እና ቴክኒክ ድጋፍ መገኛ እንደሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አዲስ አበባ ሰሞኑን ከአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ ጋር በከተማ ልማት፣ በአገልግሎት ዲጂታላይዜሽን፣ በቤት ልማት፣ በቱሪዝም፣ በስፖርት እና በሁለቱ ህዝቦች መካከል የባህልና የታሪክ ልውውጥን የሚያጠናክር የእህትማማች ከተማ ስምምነት አድርጋለች፡፡

ከተማዋ፣ የዓለም አቀፍ “የእህት ከተሞች” ትስስርን እንደ ቴክኖሎጂ ሽግግር ድልድይ በመጠቀም፣ የወረቀት ላይ ስምምነቶችን ወደ ተግባር እየለወጠች ነው፡፡ ከተማዋ  ከአውሮፓዋ ሊዮን ከተማ ጋር ካላት በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ትስስር በተገኘ ልምድ እና ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት በወሰደው ቆራጥ እርምጃ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ሰፊ የኮሪደር እና የወንዞች ዳርቻ ልማት እየተተገበረ እና ሰውን ማዕከል ያደረገ ለውጥ እየተመዘገበ ይገኛል።

የአዲስ አበባ እህት ከተማ የሆነችው ኪጋሊ አገልግሎቶችን መቶ በመቶ ዲጂታላይዝ በማድረግ ቀዳሚ ከተማ መሆኗ ይታወቃል። አዲስ አበባም ይህንን ተሞክሮ በመውሰድ ወረቀት አልባ አሰራርን፣ ዲጂታል መታወቂያን እና የተሳሰረ የህክምና መዝገብን ተግባራዊ እያደረገች እና ፅዱ፣ ውብና ለኑሮ ተስማሚ ከተማነቷን እያረጋገጠች ነው፡፡

ከዲጂታላይዜሽን አንፃርም የወሳኝ ኩነት፣ የንግድ ፈቃድ እና የቤት ግብር ክፍያዎች በኦንላይን እንዲከናወኑ ተደርጓል። የመንገድ ደህንነትን በቴክኖሎጂ ለመቆጣጠር እና የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ በተደረገው ትብብር አዲስ አበባ የብሉምበርግ ዓለም አቀፍ ሽልማት ባለቤት መሆኗም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ከአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ ጋር የተፈረመው ስምምነት በከተማ ልማት፣ በአገልግሎት ዲጂታላይዜሽን፣ በቤት ልማት፣ በቱሪዝም (ስፖርት ቱሪዝምን) ጨምሮ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የባህልና የታሪክ ልውውጥን የሚያጠናክር መሆኑን አመልክተዋል።

ባኩ በካስፒያን ባህር ምዕራባዊ የባህር ዳርቻ ላይ የምትገኘው የአዘርባጃን ዋና ከተማ  ናት። በካውካሰስ ክልል ውስጥ ካሉት እጅግ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ካላቸው ከተሞች አንዷ ስትሆን የአዘርባጃን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የባህል ማዕከል ሆና ታገለግላለች። ባኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘመናዊና ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎቿ፣ በኃይል ኢንዱስትሪ፣ በተራቀቁ መሠረተ ልማቶቿ እና በታላላቅ የከተማ ትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክቶቿ ትታወቃለች።

በቅርብ አሥርት ዓመታት ውስጥም ከተማዋ በትራንስፖርት፣ በአረንጓዴ ቦታዎች፣ በዲጂታል መሠረተ ልማቶች፣ በቱሪዝም እና በሥነ ሕንፃ ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማድረግ ራሷን ወደ ዘመናዊ የከተማ ማዕከልነት ቀይራለች። ባኩ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ያስተናገደቻቸው እንደ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ኮንፈረንሶች እና የከተማ ልማት መድረኮችን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችም ተፈላጊነቷን የበለጠ ጨምረውላታል ይላል የአዘርባጃን ብሔራዊ የከተማ ፎረም እ.ኤ.አ ጥቅምት 2025 ይፋ ባደረገው መረጃ፡፡

ባኩ ከሂዩስተን፣ ኔፕልስ፣ ሳራጄቮ፣ ኢዝሚር፣ ሞስኮ እና ሌሎችም ከተሞች ጋር ሰፊ ዓለም አቀፍ እህትማማችነትን መስርታለች፡፡ በአዲስ አበባ እና በባኩ መካከል የተደረገው የእህትማማች ስምምነትም የሁለቱን ከተሞች ከፍታ የሚያሳይ መሆኑን የከተማ ልማት ባለሙያና አማካሪ ኢንጂኒየር በሱፈቃድ አየለ ይናገራሉ፡፡

አዲስ አበባ ልክ እንደ ባኩ ሁሉ፣ ግዙፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች፣ የከተማ እድሳት ፕሮግራሞች፣ የዲጂታል አገልግሎት ማሻሻያዎች፣ ዘመናዊ የትራንስፖርት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት እና ለቱሪዝም ትልቅ ቦታ በመስጠት ለምታከናውነው ልማት ስምምነቱ ተጨማሪ አቅም እንደሚኖረው ኢንጂኒየር በሱፈቃድ አብራርተዋል። ቀደም ሲል በ2026፣ አዘርባጃን ኢትዮጵያ በ2027 እንድታስተናግድ የሚጠበቀውን የCOP32 ዝግጅት ለመደገፍ ቃል መግባቷንም አስታውሰዋል፡፡

አዲስ አበባ የኮሪደር ልማት እና የዲጂታል አስተዳደር ፕሮጀክቶችን እያሰፋች ስትሄድ ተፈላጊነቷ እየጨመረ መጥቷል የሚሉት ኢንጂኒየሩ፣ በዚህም ዓለም አቀፍ ታላላቅ ጉባኤዎችን በማስተናገድ፣ በቅርስ ቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች መዳረሻነቷ ከፍ እያለም መጥቷል፡፡ ለአብነትም አዲስ አበባ በ2017 ዓ.ም ብቻ 150 ያህል ታላላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በስኬት በማከናወን ተመራጭ የኮንፍረስ ቱሪዝም መዳረሻ መሆኗን አረጋግጣለች፡፡

ሰሞኑን በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው የልዑካን ቡድን በአዘርባጃን የካስፒያን የባህር ዳር የተቀናጀ የከተማ ልማት ፕሮጀክት (Sea Breeze Project) መጎብኘቱን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅሕፈት ቤት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት አዘርባጃን በአሁኑ ወቅት ካስመዘገበችው ከፍተኛ ዕድገት ጎን ለጎን የከተማ መልሶ ማልማት ሥራዎችን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ አሮጌ መንደሮችን በማንሳት አድሳለች፡፡ ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቦታዎችንም ለይቶ የማልማት ስትራቴጂ እየተከተለች ነው፡፡

በ16 ዓመታት ጊዜ ውስጥም የሚጠናቀቁ 50 ሺህ መኖሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎችና ተያያዥ የልማት ሥራዎች በ‘Sea Breeze ፕሮጀክት’ ሥር በስፋት እየተገነቡ እንደሚገኙና የግሉ ዘርፍም ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት በከፍተኛ ደረጃ እየተሳተፈ ይገኛል። አዲስ አበባም፣ በየዓመቱ 100 ሺህ ቤቶችን እና ተያያዠ ልማቶችን ለመገንባት ርብርብ እያደረገች ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያረጁና የተጎሳቀሉ አካባቢዎችን የማደስ ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በአግባቡ ጥቅም ላይ ያልዋሉ እንደ የጫካ ፕሮጀክት፣ ገላን-ጉራ እና አዲስ ቱሞሮ ያሉ አካባቢዎችን በመጠቀም አዲስ ከተማ የመገንባት ያህል ምቹ የልማትና የመኖሪያ ስፍራዎችን ለመፍጠር እየተሠራ ነው።

ይህ መጠነ-ሰፊ የቤት ልማትና የከተማ ማደስ እንቅስቃሴ በዋናነት የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለልና መዲናዋን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የታለመ ነው፡፡ በቀጣይነትም በላቀ ጥረትና በልማት ልኅቀት አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ በማድረግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን ግንባር-ቀደም የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም በመረጃው ተመላክቷል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review