AMN- ሐምሌ 13/2018 ዓ.ም
ሐምሌ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የነበረው ድባብ እጅግ የተለየ ነበር።
በአራቱም ማዕዘን የቆሙ የትግራይ ተወላጆች፣ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና የከተማዋ ነዋሪዎች ዓይኖች ሁሉ “አፈሳ ይቁም፤ ሰላም ይስፈን፣ ልጆቻችንን ተውልን!” የሚል አንድ ተመሳሳይ መልዕክት ያስተጋቡ ነበር።
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሐሳቧን ያጋራችው እናት፣ በቁጭትና በሐዘን በተሞላ ድምፅ እያነባች፣ “ቀደም ብዬ ወንድሜን አጥቻለሁ፤ አሁን ደግሞ ሌላኛው ታፍኖ ወዴት እንደተወሰደ አላውቅም ስትል ገልፃለች።

የት እንደገባ፣ ምን እየሆነ እንዳለ እንኳ የምሰማበት ምንም ዓይነት መንገድ የለኝም” በማለት የደረሰባትን መከራ ታስረዳለች።
በእሷ ዙሪያ የነበሩ ሌሎች እናቶችም በተመሳሳይ የሐዘን ስሜት ተውጠው እንባቸውን ሲያዘሩ ተስተውለዋል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ሕገ-ወጥ ቡድን፣ በኃይል ከትምህርት ቤት፣ ከመኖሪያ ቤት እና ከመንገድ እየለቀመ የወሰዳቸው ሕፃናትና ወጣቶች የት እንደደረሱ ማንም የሚያውቅ የለም።

ገና የእናትን ፍቅር ያልጠገቡ የ15 ዓመት ታዳጊዎች፣ ለውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዲሆኑ ወደ ሱዳንና ሌሎች አካባቢዎች እንደ አሻንጉሊት እየተሸጡ መሆኑንም የሰልፉ ተሳታፊዎች በምሬት ያስረዳሉ።
አንድ የሰልፉ ተሳታፊ አባት በበኩላቸው፣ በቁጭት ሲናገሩ፤ “ኢትዮጵያ ራሷን በራሷ አትወጋም” ካሉ በኋላ፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ሕገ-ወጥ ቡድን የትግራይን እናቶች እያሳደደ እና የክልሉን ልጆች ለእሳት እየማገደ ለባዕድ ወገን ደጋፊ መሆኑን አብራርተዋል።
በዕለቱ አደባባዩ ላይ የተንጸባረቀው ዋናው መልዕክት፣ የትግራይ ሕዝብ የሰላም ሕዝብ መሆኑንና ጦርነት እንደማይፈልግ የሚገልጽ ነው።

ነገር ግን የቤተሰብ መበታተን፣ የወጣቶች አፈሳ እና የእናቶች ዕንባ በክልሉ ሰላምን እየያደበዘዘው በመሆኑ “በቃ! ጦርነት ይብቃ!” የሚለው ጩኸት በአደባባዩ በስፋት አስተጋብቷል።
ልጆቻችንን ተዉልን፤ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ አድርጉ፣ ጦርነቱ ይብቃ! የሚለው ይኸው የለቅሶ ድምፅ፣ አፋጣኝ ምላሽ የሚሻ ሰፊ የሰብአዊነት ጥያቄ ሆኖ አልፏል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ