AMN – ሚያዝያ 20/2018 ዓ.ም
የብስክሌት ስፖርት ከሜዳ በራቁ ተራራማ ስፍራዎች ተወጥቶ ወደ ከተማ እምብርት፣ ወደ ህዝብ መሀል ሲመጣ ልዩ ድምቀት ይፈጥራል፡፡
ይህ በዓለምአቀፉ የብስክሌት ማህበር (UCI) እውቅና ያገኘው የ”ሲቲ ማውንቴን ባይክ ኢሊሚኔተር” ውድድር፣ ከተሞችን የውድድር መድረክ በማድረግ የከተማ ቱሪዝምንና ስፖርታዊ ስሜትን የሚያቀናጅ ድንቅ ኩነት ነው፡፡
የማውንቴን ባይክ ኢሊሚኔተር (XCE) ውድድር በይፋ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ2012 ሲሆን፣ አላማውም የተራራ ላይ የብስክሌት ውድድርን ይበልጥ ለተመልካች ቅርብና አዝናኝ ማድረግ ነበር።
ውድድሩ በአጭር ርቀት (ከ500 ሜትር እስከ 1 ኪሎ ሜትር) ላይ የሚደረግ ሆኖ፣ ሳይክል ጋላቢዎች የተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ መሰናክሎችን አልፈው በመጨረሻው መስመር ፈጣን ሆነው ለመገኘት የሚፋለሙበት ነው።

ይህ ውድድር እስከ ዛሬ ድረስ እንደ አንትወርፕ (ቤልጂየም)፣ ባርሴሎና (ስፔን)፣ ፓሪስ (ፈረንሳይ)፣ ኢንዶኔዢያ (ፓላንካ ራያ) እና ሳኦ ፓውሎ (ብራዚል) ባሉ ታዋቂና ታሪካዊ የዓለም ከተሞች በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል፡፡
ውድድሩ በተከናወነባቸው ከተሞች ሁሉ ትልቅ አሻራ ጥሎ የሚያልፍ ዘርፍ ነው ፡፡ የገፅታ ግንባታ (Branding) ውድድሩ በቀጥታ ስርጭት ለሚሊዮኖች ስለሚተላለፍ፣ የከተሞቹን ውበት፣ ታሪካዊ ህንጻዎችና ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች ለዓለም ያስተዋውቃል፡፡
የቱሪዝም ፍሰት: በሺዎች የሚቆጠሩ ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞችና ስፖርት ወዳድ ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ እንዲመጡ በማድረግ የሆቴልና የጉብኝት ገቢን ያሳድጋል፡፡ ውድድሩን ተከትሎ የሚመጡ ስፖንሰርሺፖች ፣ የአገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችና የሥራ ዕድሎች ለከተማዋ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ይሆናሉ፡፡
አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች አማካኝነት የብስክሌት መንገዶችን፣ ሰፋፊ የእግረኞቸ መንገድና አረንጓዴ ስፍራዎችን እያስፋፋች ትገኛለች፡፡ ይህ ውድድር በከተማዋ መካሄዱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያስገኝላታል፡፡
አዲስ አበባ ያከናወነችው እጅግ ዘመናዊና ማራኪ የኮሪደር ልማት እና የወንዞች ዳርቻ ልማት ለዓለምአቀፍ ስፖርት ምቹ መሆኑን በተግባር ለማሳየት ታላቅ አጋጣሚ ነው፡፡ ይህም “ስማርት ሲቲ” የመገንባት ጉዞዋን ያረጋግጣል። የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ፣ እንዲህ ያሉ ዓለምአቀፍ ውድድሮችን ማስተናገዷ አዲስ አበባን ከዲፕሎማሲ ባለፈ የስፖርት ቱሪዝም መዳረሻ ያደርጋታል፡፡

የብስክሌት ስፖርት “አረንጓዴ ትራንስፖርትን” የሚያበረታታ በመሆኑ፣ ከተማዋ ለተመጣጣኝ የአየር ንብረትና ለጤናማ የአኗኗር ዘይቤ የምታደርገውን ጥረት ይደግፋል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች በውድድሩ ላይ በመሳተፍና ዓለምአቀፍ ተሰጥኦዎችን በአካል በመመልከት ለብስክሌት ስፖርት ያላቸው ፍቅር እንዲጨምር ያደርጋል፡፡
የሲቲ ማውንቴን ባይክ ኢሊሚኔተር ውድድር ከአዲስ አበባ የለውጥ ጉዞ ጋር ፍጹም የተጣጣመ ኩነት ነው፡፡
ይህ ስፖርት በከተማችን አደባባዮች ላይ ሲከናወን፣ አዲስ አበባን በዓለም ካርታ ላይ በስፖርትና በውበት ደምቃ እንድትታይ የሚያደርግ ትልቅ የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ድል ይሆናል፡፡
ይህንን በዓይነቱ ልዩ የሆነና በአዲስ አበባ ሲካሄድ የመጀመሪያ የሆነውን የሲቲ ማውንቴን ባይክ ኢሊሚኔተር ውድድር አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ባሉት የቴሌቭዥን እና የራዲዮ እንዲሁም የዲጂታል ሚዲያ አማካኝነት ወደ ተመልካች ለማድረስ የሚያስችለውን ስምምነትም መፈፀሙ ይታወቃል፡፡
በያለው ጌታነህ