AMN – ሐምሌ 14/2018 ዓ.ም
በከተሞች ፈጣን እድገትና በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተፅዕኖዎች ምክንያት የሚከሰት የኑሮ ውድነት የበርካታ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ከተሞች ዋነኛ ፈተና እንደሆነ ይጠቀሳል። ይህ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ አዲስ አበባንም የሚነካ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዜጎችን የኑሮ ጫና መቀነስ ከቀዳሚ ሥራዎቹ አንዱ አድርጎ እየሰራ ይገኛል። የከተማ አስተዳደሩ የሕብረተሰቡን ቀጥተኛ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም የሚያስችሉ ዘርፈ-ብዙ የድጎማና የልማት መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
በበጀት ዓመቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ከኑሮ ጫና ለመጠበቅ ከ8.2 ቢሊዮን ብር በላይ ቀጥተኛ ድጎማ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት ያመላክታል።

ይህ ከፍተኛ የበጀት ድጎማ በዋናነት በትራንስፖርት ፣ በጤና መድህን ፣ በቋሚ የሸቀጦች አቅርቦት ፣ በትምህርት ቤት ደንብ ልብስ እና በተማሪዎች ምገባ ላይ እንዲውል ነው የተደረገው።
በመንግስት ድጎማ የሚቀርቡ መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን በፍትሃዊነት ለነዋሪው ለማዳረስ በተደረገው ጥረት 200 ሺህ434 ኩንታል ስኳር እና ከ10.1 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለህብረተሰቡ በትስስር እንዲሰራጭ ተደርጓል።
የግብርና ምርቶች አቅርቦትን በዘላቂነት ለመደገፍ የከተማ አስተዳደሩ የተዘዋዋሪ ብድር ፈንዱን ወደ 825 ሚሊዮን ብር በማሳደግ ለ11ዱም የህብረት ስራ ዩኒየኖች ድጋፍ ማድረጉ የአቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
አላስፈላጊ ደላላ ተኮር የዋጋ ጭማሪዎችን ለማስቀረት የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ቁጥር ወደ 259 እንዲያድግ ተደርጓል። ከዚህ ጎን ለጎን የግብርና ምርቶች በስፋትና በፍጥነት ወደ ከተማዋ እንዲገቡ በ15.9 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ 7 ዘመናዊ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት በከተማዋ አምስት መግቢያዎች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል።

እነዚህ ማዕከላት 432 የምርት ማከማቻ መጋዘኖችንና ከ1ሺ 300 በላይ የጅምላና የቸርቻሮ ሱቆችን በመያዝ የምርት ፍሰቱን እያቀላጠፉ ይገኛሉ።
የኑሮ ውድነት በቤተሰብ ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ ከተከናወኑ አርአያነት ያላቸው ተግባራት መካከል የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ወደ 1 ሚሊዮን ለሚጠጉ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ጥራት ያለው ምግብ እንዲያገኙ አድርጓል።
ይህ መርሃ ግብር የተማሪዎችን ትምህርት ማቋረጥና ማርፈድ ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ከመቀነሱም በላይ፣ ለ20 ሺህ እናቶች የሥራ እድል በመፍጠር ተጨማሪ የኢኮኖሚ ድጋፍ መሆን የቻለ ነው።
ጧሪ የሌላቸውንና አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ በተዘረጉ 30 የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላትም በቀን አንድ ጊዜ በአማካይ ለ35 ሺህ ዜጎች የምገባ አገልግሎት እየቀረበ ይገኛል።

ከተማ አስተዳደሩ በ2018 በጀት ዓመት ያስመዘገባቸውን ውጤቶችን በማጠናከር፣ በ2019 በጀት ዓመትም የነዋሪው ቀዳሚ ጥያቄ የሆነውን የኑሮ ውድነት መቋቋም የሚያስችሉ እና የገበያ መረጋጋትን የማስፈን ሥራዎች ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫው መሆናቸውን አስታውቋል።
ለዘላቂ ልማትና ድህነት ቅነሳ የሚውለውን የበጀት ድርሻ ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት 47% ወደ 71% ማሳደግ መቻሉ፣ የከተማዋን የወደፊት ብልጽግና የሚያረጋግጥና ለዜጎች ማህበራዊ ፍትህ የሚያሰፍን ጠንካራ መደላደል እንደሚሆንም ይታመናል።
በታደሠ ሽፈራው