AMN- ነሐሴ 9/2018 ዓ.ም

ሻዕቢያ ፣ ህገ-ወጡ ህወሓት ፣ አሸባሪው ሸኔ እና ጽንፈኛው ፋኖ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ ተሸክመው ሀገር ለማተራመስ ዳግም ጥምረት መፍጠራቸውን የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ሰለሞን ተፈራ ገለጹ።
ምሁሩ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ የቡድኖቹን እውነተኛ ጸባይና ታሪካዊ ግንኙነት አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት ጸረ-ሰላም ኃይሎቹ የጋብቻ ውል ማደስ በሚመስል መልኩ አዲስ ጥምረት በመፍጠር ላይ መሆናቸውን ያነሱት አቶ ሰለሞን፣ የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የባህር በር ጥያቄን ለማኮላሸት ተብሎ በ1960ቹ የተፈጠረው የሻዕቢያ ፣ ግብጽ እና የህገ ወጡ ህወሓት እኩይ ጋብቻ ላይ ጽንፈኛው ፋኖ እና አሸባሪው ሸኔን መጨመሩን ጠቅሰዋል፡፡
የሻዕቢያ እና የግብፅ ግንኙነት ሲገልጹ፣ የሻዕቢያ መንግሥት የኢትዮጵያን ሃብት በመዝረፍ ለመጠቀም ሲፈልግ፣ የግብፅ መንግሥት ደግሞ የኢትዮጵያን ሀብት በብቸኝነት ለመቆጣጠር ያለመ ግንኙነት እንዳላቸው ገልፀዋል።
ሻዕቢያ እና የህገ-ወጡ ህወሓት በአሁኑ ወቅት የትግራይን ሕዝብ እንደ መሸሻ እና መነገጃ በመጠቀም፣ በዶላር እየነገዱበት የሚገኙ ኃይሎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሻዕቢያ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ የፌዴራል መንግስት ጦርነት ማቆሙ እንዳስኮርፈውና በዚህም ከሌሎች ኃይሎች ጋር ጥምረት በመመሥረት ኢትዮጵያን ለማወክ ወደ እንቅስቃሴ መግባቱን ጠቅሰዋል።
ህገ-ወጡ ህወሓት እና የአሸባሪው ሸኔ በየራሳቸው ማህበረሰብ ስም እየነገዱ ህዝብን ለስቃይ የዳረጉ ቡድኖች መሆናቸውንም አንስተዋል።
በታሪክም በ1983 ዓ.ም ህገ-ወጡ ህወሓት ከኦነግ ጋር አብሮ ታግሎ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ፣ የኦነግን ሠራዊት አታሎ ወደ ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ በማሰባሰብ በክህደት በጅምላ ያስጨረሰበት ታሪክ እንዳለው አውስተዋል።
አሁን ላይ እነዚህ ቡድኖች ያንን ታሪክ ወደ ጎን በመተው ዳግመኛ መጣመራቸውን በመጥቀስም፣ ሕዝቡ የእነዚህን ኃይሎች እውነተኛ ጸባይ ሊረዳ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ሰለሞን ተፈራ፣ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንድትሆን የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር በማጣቷ ምክንያት ለበርካታ ችግሮች መጋለጧን እና የተፈጥሮ ሀብቷን በሙሉ አቅም መጠቀም ያልቻለች ሀገር መሆኗን በመጥቀስ ኢትዮጵያ የምታነሳው ፍትሃዊ የባህር በር ጥያቄ የህልውና እና የልማት ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ