AMN – ነሐሴ16/2018 ዓ.ም
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያከናወናቸው ተግባራት በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚሻገር ታሪካዊ አሻራ የሚያኖሩ እና ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገለጹ።
ፕሬዚዳንቱ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ፣ የምክክር ሂደቱ በተፎካካሪና በተቃራኒ እይታዎች መካከል የበሰሉ አዳዲስ ሐሳቦች እንዲወለዱና የጋራ ዕጣ ፈንታን በአንድነት ለመወሰን መደላደል የፈጠረ ነው ብለዋል።
እንዲሁም የቁጣና የጽንፈኝነት ስሜትን በማስወገድ ውይይቶች በምክንያታዊነትና በሰከነ መንፈስ እንዲመሩ አስችሏል ነው ያሉት ኘሬዝደንቱ።
የፖለቲካ ምህዳሩ ከተቃርኖና ከጠላትነት ወጥቶ በይቅርታ፣ በመከባበርና በመደጋገፍ ላይ እንዲመሠረት ማድረግ የተቻለበት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
ምክክሩ የፖለቲካ ልምምዳችን ከኃይልና ከአመፅ ተላቆ በሰላም፣ በመደማመጥና በነፃ የሐሳብ ፍጭት ላይ እንዲያተኩር ትልቅ መንገድ የከፈተ ሲሆን፤ በማኅበራዊ አውድ ውስጥ የሚነገሩ የፖለቲካ ንግግሮች ሰከን እንዲሉና የመከባበር ባህል እንዲጎለብት አድርጓል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚሰነዘሩባትን “ልትፈርስ ነው” ወይም “መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች” የሚሉ የፖለቲካ ትረካዎችንና የሥጋት ቃላት በመሻገር፣ በጠንካራ ማኅበራዊ ትስስሯና በዘመናት ሥልጣኔዋ ፈተናዎችን በጋራ የመመከት አቅም እንዳላት አንስተዋል።
የምክክር ሂደቱ ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው ላደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ሂደቱን በባለቤትነት ለደገፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል።
በተጨማሪም የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አርሶ አደሮች እና የሲቪል ማኅበራት በንቃት የተሳተፉበት ይኸው ሂደት ትልቅ ስኬት እንዲመዘገብ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ገለፀዋል።
በበረከት ጌታቸው