AMN- መስከረም 27/2019 ዓ.ም

በ”መደመር” እሳቤ ተመሥርተን በለውጡ ጊዜ የሞከርናቸው ተግባራት አስደናቂ ውጤት አምጥተውልናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በ7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመስረቻ 1ኛ መደበኛ ጉባዔ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሀገሪቱን ውስብስብ ችግሮች በውጭ ሀገር ልምዶች ብቻ ለመፍታት መሞከር አዋጭ እንዳልሆነ አስገንዘብዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የየወቅቱ መሪዎች አቋራጩን በመምረጥ የውጭ ሀገር ዕሳቤዎችን በግድ በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን ሲጣጣሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ያላትን የሥልጣኔ ወረት በመጠቀምና የሥነ መንግሥት እሴቶቿን በማዘመን ጠንካራና ገናና ሥልጣኔ መገንባት እንደምትችል ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያን ለሌሎች ዕሳቤዎች ከመቀየር ይልቅ፣ ለኢትዮጵያ ሲባል የሌሎችን ዕሳቤ አቃንቶ መቀበል ተገቢ አካሄድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለፉት ዓመታት መደመር የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ግንባታ እውን ለማድረግ እንደሚያስችል በተግባር መረጋገጡን ገልጸዋል።
ከፋፋይና ጠቅላይ ዕሳቤዎች በኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲተኩ በመደረጉ፣ አስደናቂ ውጤቶች መምጣታቸውን እና የሀገሪቱን የፖለቲካ መልክ መቀየር መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ከዚህ ቀደም ዳርና መሐል፣ እንዲሁም ዋናና አጋር ተብሎ የተከፋፈለውን የፖለቲካ ትርክትን በመደመር ዕሳቤ ወደ ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና አብሮነት ማምጣት መቻሉንም አንስተዋል።
በበረከት ጌታቸው