ኢትዮጵያ የውበት መጠበቂያ ምርቶች ለማምረት ሜርኩሪ ኬሚካል ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚከለክለው የሚናማታ ዓለም አቀፍ ስምምነት ትግበራ እንዲሳለጥ ቁርጠኛ መሆኗን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ ገለጹ።
የቆዳ ውበትን ለማስጠበቅ በሚመረቱ ምርቶች ላይ የሚጨመረው ሜርኩሪ የተሰኘው ኬሚካል ለሰው ጤናና አካባቢ ብክለት መጨመር አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ።
የሜርኩሪ ኬሚካል በምርቶቹ ውስጥ እንዳይጨመር ለማደረግ የወጣውን ዓለም አቀፍ የሚናማታ ሥምምነት በርካታ አገራት ፈርመዋል።
ሥምምነቱ በአፍሪካ አገራት እንዲተገበር ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱ የተገለጸ ሲሆን በፕሮጀክቱ ቀጣይ ትግበራ ዙሪያ ትኩረት ያደረገ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በአውደ ጥናቱ ላይ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት እና የልማት አጋሮችን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ13 የአፍሪካ አገራት የሚተገበር ሲሆን ሜርኩሪ የተጨመረባቸው የቆዳ ማስዋቢያ ምርቶች ዝውውር፤ ንግድና አቅርቦት ሰንሰለትን መቁረጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ሜርኩሪ የተጨመረባቸው ምርቶችን መቀነስ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች እንዲኖሩ ማድረግ እና ቁጥጥርን ማጠናከር፣ የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ከዓላማዎቹ መካከል ናቸው።
የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ እንዳሉት፤ ሜርኩሪ በአካባቢ ብቻ ሳይሆን በሰው ጤናና ቀጣይ ትውልድ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ነው፡፡
ሴቶችና ታዳጊ ህጻናት የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆናቸውን ገልጸው፤ ሜርኩሪ የተጨመረባቸው ምርቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅብናል ሲሉ መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡