በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት 5 ወራት ከ5 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ከምዝበራ ማዳን መቻሉን የአዲስ አበባ ስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ፣ ለአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ኤፍ ኤም 96.3 ራዲዮ እንዳስታወቁት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት 5 ወራት ብቻ ከሙስናና ብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ 394 ጥቆማዎች ለኮሚሽኑ እንደደረሰው ተናግረዋል፡፡
የቀረቡ ጥቆማዎችን በመመርመርም 39 የሙስና ጉዳይ እንደሌላቸው፣ 17 ደግሞ የሙስና ጉዳይ ስላለባቸው ምርመራ እንዲደረግባቸው የመመርመር ስልጣን ለተሰጠው አካል መላኩን ነው ኮሚሽነሩ ያመለከቱት፡፡
ባለፉት 5 ወራት ብቻ ሊመዘበር የነበረን 5 ሺህ 483 ካሬ ሜትር ቦታ ማዳን መቻሉንም ነው ኮሚሽነሩ ያስታወቁት፡፡
ኮሚሽኑ ባደረጋቸው የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ስራዎችም፣ በተለያዩ መንገዶች ሊዘረፍ የነበረን ከ402 ሚሊዮን 773 ሺህ ብር በላይ ማትረፍ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
ምዝበራ ሊደረግባቸው የነበሩት ሀብቶችም መሬት፣ ልዩ ልዩ ብረታ ብረቶች፣ መስታውቶች፣ የቀበሌ ቤቶች፣ መመሪያን ያልተከተለ የቅጥርና የሰራተኛ ምደባ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በሽመልስ ታደሰ