“የፋይናንስ እምርታ በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የፋይናንስ ኮንፈረንስ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የካፒታል ገበያ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ያለውን ፋይዳ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፤ አዳዲስ የኢኮኖሚ ለውጦችን ከመቀበል አኳያ የሚታዩ የአመለካከት ክፍተቶችንና የገበያው መመስረት የሚፈጥረውን ዕድል በዝርዝር ዳስሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ በምሁራንና በኩባንያ ባለቤቶች ዘንድ የሚታየውን አዲስ ነገር የመሸሽ ዝንባሌ ተችተዋል።
አዲስ ነገር ሲመጣ አውቀንም ይሁን ሳናውቅ የማራከስ፣ የመሸሽና ያለመጋፈጥ ሁኔታ ይታያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይም እናውቃለን የሚሉ ወገኖች መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ለውጡ አያስፈልግም የሚል አቋም ማንፀባረቃቸው የሚያሳዝን መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም በፍጥነት እየተለወጠ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዛሬ የምንፈጥረው አሰራር ልጆቻችን ነገ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩበት ምቹ አውድ መሆኑን አንስተዋል ።

የካፒታል ገበያን ምንነት ሲያብራሩም፣ ተቋሙ ለኢኮኖሚው አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ቁሳቁሶችን በገንዘብ መግዛት ቢቻልም፣ ገንዘብ ፈላጊዎች ግን ገንዘብ ሊገዙ የሚችሉበት አውድ አልተመቻቸም ነበር በማለት የነበረውን ክፍተት አስረድተዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ የካፒታል ገበያ አንድ ሰው ጠቃሚ የንግድ ሃሳብ ሲኖረው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሃሳቡ ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ የሚያገኝበትን መንገድ ያመቻቻል እንዲሁም በተበዳሪና በአበዳሪ መካከል ጠንካራ ተቋማዊ መተማመን እንዲፈጠር ያደርጋል ብለዋል።
የብዙ ሀገራት የኢኮኖሚ መሰረት የሆነው ይህ ተቋም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ሳይመሰረት መቆየቱ ተገቢ እንዳልነበረም ተናግረዋል።
የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ ስራ ከጀመረ ጥቂት ዓመታት ማስቆጠሩንና በአሁኑ ወቅት በጣም ጥሩ መሠረት መያዙን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ተቋሙ ከአሰራር ባለፈ ብቃት ያላቸውን በርካታ ወጣት አመራሮች በማፍራት ረገድ ትልቅ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑንም በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል።
በአስማረ መኮንን