AMN – የካቲት 26 ቀን 2018 ዓ.ም
የካራማራ ድል “ከዘላለም ባርነት የአንድ ቀን ነፃነት” በሚል አዋጅ የጠላትን ወረራ ለመቀልበስ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ጠላትን አሸንፈው ሉዓላዊነታቸውን ያስከበሩበት ነው፡፡
የዚያድ ባሬ መንግስት በ1960ዎቹ መጨረሻ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ጦርነት የሚፈነዳ ከሆነ ሶማሊያ ውጊያውን በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ በርካታ መልካም አጋጣሚዎች ይኖሯታል በማለት ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ወረራ ፈጸመ፡፡
ወረራው የተፈጸመባት ኢትዮጵያም ሚያዝያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሊቀመንበር ሌተናል ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም በኩል የእናት ሀገር ጥሪ አሰማች።
ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉረት የታሪክ ባለሙያ አቶ ንጉሱ መኮንን፣ ወረራው ልክ እንደ አድዋ ሁሉ “ከዘላለም ባርነት የአንድ ቀን ነፃነት” የሚል አዋጅ በማስነገር ወረራውን መቀልበስ አለብን በማለት የክተት አዋጅ እንደታወጀ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን በአፍሪካም ሆነ በዓለም ታሪክ ውስጥ የተሸናፊነት ታሪክ የላትም፡፡ የተከፈለው መስዋትነት ተከፍሎ የዚያድ ባሬ መንግስት መሸነፍ እና ዳር ድንበራችንን ማስከበር አለብን በሚል 300 ሺህ የሚደርሱ ሚሊሻዎችን በማሰልጠን የኢትዮጵያን ወኔ በመታጠቅ ከካራማራ ተራራ ላይ የካቲት 26/ በ1970 ዓ.ም ድሉ መበሰሩን አስታውሰዋል።
እንደ አቶ ንጉሱ መኮንን ገለጻ የካራማራው ወረራ ከ1928ቱ የጣሊያን ወረራ በኋላ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ላይ የተቃጣ ትልቅ አደጋ ሆኖ ተመዝግቧል።
48ኛው የካራማራ ድል መታሰቢያ በዓልም አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው የኢትዮ-ኩባ የወዳጅነት ፓርክ ተከብሯል፡፡
በካራማራው ድል ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጎን ኩባውያንም ተሰልፈው ታላቅ ጀብዱ መፈጸማቸው ይታወሳል።
በትዝታ መንግስቱ