በኬንያ በተከሰተ ከባድ የጎርፍ አደጋ የ42 ሰዎች ሕይወት አለፈ

You are currently viewing በኬንያ በተከሰተ ከባድ የጎርፍ አደጋ የ42 ሰዎች ሕይወት አለፈ

AMN – የካቲት 30/2018 ዓ.ም

በኬንያ ለተከታታይ ቀናት የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ፣ ቢያንስ የ42 ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና ከ50 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

የኬንያ የሕዝብ አገልግሎትና ልዩ ፕሮግራሞች ሚኒስትር ጂኦፍሬይ ሩኩ እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ ፖሊስ ከአርብ ጀምሮ 42 ሞት መመዝገቡን የገለጸ ሲሆን፣ ከሟቾቹ ውስጥ 26ቱ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ መመዝገቡን እና ጎርፉ መኖሪያ ቤቶችን በማጥለቅለቅና ተሽከርካሪዎችን በመውሰድ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን የአልጄዚራና የቲአር ቲ ዘገባ ያስረዳል።

የጎርፍ አደጋው መንስኤ ድንገት በጣለው ከባድ ዝናብ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ አደጋው የተከሰተው አርብ ሌሊት አብዛኛውን የኬንያ ክልል የመታውን ኃይለኛ ዝናብ ተከትሎ የመጣ ድንገተኛ ጎርፍ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ጎርፉ ባስከተለው አደጋ በርካታ መንገዶችና ድልድዮች በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ ሲሆን፣ ይህም የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አቅርቦት ሥራውን በእጅጉ አዳጋች እንዳደረገው ተገልጿል።

የሀገሪቱ የአየር ንብረት ባለሙያዎች በቀጣዮቹ ቀናት ተጨማሪ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ትንበያቸውን ያስቀመጡ ሲሆን፣ ይህም የጎርፍ አደጋውን ይበልጥ ሊያሰፋው እንደሚችል እና ዜጎችም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እያሳሰቡ ይገኛሉ።

በኬንያ የሚገኙ ረድኤት ድርጅቶችና የመንግሥት የደህንነት አካላት ተጎጂዎችን ለመታደግ ርብርብ እያደረጉ መሆኑም ተገልጿል ።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review