AMN መጋቢት 8/2018
የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የአፍሪካን ትርክትና ህልም በጋራ ለመቅረፅ ገንቢ ሚና እንዳላቸው የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍጹምእሸት ሽመልስ ገለጹ።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ስብሰባ በመጭው ሚያዚያ 29 እና 30 ቀን 2018 ዓ.ም በዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ስብሰባ ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በንቃት መሳተፍ በሚችሉባቸው ዕድሎች ዙሪያ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር ውይይት ተደርጓል።
የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍጹምእሸት ሽመልስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካን ገንቢ ትርክት ለመገንባት በአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እጅ ነው።
አፍሪካ የትርክት ተጎጂ መሆኗን ገልጸው፤ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ የአፍሪካ ትርክት ለመቀየር የተቋቋመ አፍሪካዊ ሚዲያ መሆኑን ተናግረዋል።
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ መነሻው ኢትዮጵያ መዳረሻው አፍሪካ ነው ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ከማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጋር በመተባበር የአፍሪካን ትክክለኛ ገፅታ ለዓለም እንደሚያስተዋውቅ ገልጸዋል።
በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ፕሮሞሽን መሪ ሥራ አስፈፃሚ ተሾመ ተክሉ፤ ኢትዮጵያ የቅርስ፣ የታሪክና የባህል ባለቤት መሆኗን አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሀገራቸውን የቱሪዝም ሀብት ሲያስተዋውቁ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ኤጂኤ ቴክ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገመዳ ኦላና በበኩላቸው፤ ስብሰባው የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካን ገፅታ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የእርስ በእርስ ትብብራቸውን በማጠናከር አህጉራዊ አንድነትን መፍጠር ያስችላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ከፍተኛ የተደማጭነት ሚና በማሳደግ የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረው መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡