የፈረንሳይ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት፡- ከለጋሽ እና ተቀባይነት ወደ የጋራ ጥቅምና እኩልነት

You are currently viewing የፈረንሳይ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት፡- ከለጋሽ እና ተቀባይነት ወደ የጋራ ጥቅምና እኩልነት

AMN- ግንቦት 6/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ መካከል ያለው ግንኙነት ረጅም ታሪክ ያለው ሲሆን፣ በቅርብ ዓመታት ደግሞ ይህ ግንኙነት ከባህላዊው የዕርዳታ ድጋፍ ወጥቶ ወደ ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋርነት እና ኢንቨስትመንት እየተሸጋገረ መጥቷል። ይህ ሽግግር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ብስለት የሚያሳይ ነው፡፡

የፈረንሳይ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከአንድ ምዕተ-ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፣ በተለይም በአፄ ምኒልክ ዘመን የተገነባው የኢትዮ-ፈረንሳይ የምድር ባቡር ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው።

ፈረንሳይ ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ በትምህርት፣ በባህል እና በአርኪኦሎጂ ዘርፎች ከፍተኛ ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች።

አሁን ባለው ሁኔታ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸው ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ፈረንሳይ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ቀዳሚ የአውሮፓ የኢንቨስትመንት ምንጮች አንዷ ሆናለች።

እንደ ሜሪዲያም እና ኤሌክትሪሲቴ ዴ ፍራንሴ (ኢ ዲ ኤፍ) ያሉ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የፀሐይ እና የጂኦተርማል ኃይል ልማት ላይ በስፋት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

እንደ ብቅል ፋብሪካ ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ምርት ጀምረዋል፤ ይህም የውጭ ምንዛሬን ከመቆጠብ ባለፈ ለሀገር ውስጥ አርሶ አደሮች ገበያ ፈጥሯል። የፈረንሳይ ኩባንያዎች በሎጂስቲክስ፣ በአየር መንገድ ጥገና እና በቴክኖሎጂ ዘርፎችም ያላቸው ተሳትፎ እያደገ ነው።

የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ (ኤ ኤፍ ዲ) ቀደም ሲል ለሰብዓዊ ዕርዳታ የሚሰጠውን ትኩረት አሁን ወደ ልማት ፋይናንስ ቀይሮታል። ይህም ማለት ፕሮጀክቶች ራሳቸውን እንዲችሉ እና ለኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት እንዲሆኑ ድጋፍ ያደርጋል።

ለማሳያነትም፤ የአየር መንገድ ልማት ፋይናንስ፣ የከተማ ትራንስፖርት እና የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃ (ለምሳሌ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ጥገና እና የብሔራዊ ቤተ-መንግሥት እድሳት) ተጠቃሾች ናቸው።

ሁለቱ ሀገራት በንግድ ብቻ ሳይሆን፣ በስትራቴጂካዊ ጉዳዮችም ተቀራርበው ይሰራሉ። የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት አማኑኤል ማክሮን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያደረጓቸው ተከታታይ ጉብኝቶች፣ ግንኙነቱ ከለጋሽ እና ተቀባይነት ባለፈ በጋራ ጥቅምና እኩልነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review