AMN – ሚያዝያ 12/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚካሄደው 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ፣ ሚዛናዊ እና ተዓማኒ እንዲሆን የመገናኛ ብዙኃን የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ፤ በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ለመዘገብ ለሚፈልጉ የብዙኃን መገናኛ ተቋማትና ጋዜጠኞች የሁለተኛ ዙር የፈቃድ ጥሪ ማቅረቡን አስታወቀ።
ቦርዱ ይህንን ጥሪ ያስተላለፈው በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 እንዲሁም ተቋሙን ባቋቋመው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ዐዋጅ ቁጥር 1133/2011 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት መሆኑን ገልጿል።
ይህንን በመገንዘብ፤ የመገናኛ ብዙኃን እና ጋዜጠኞች በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ለመዘገብ የሚያስችላቸውን የፍቃድ ጥያቄ ለቦርዱ እንዲያቀርቡ የ2ኛ ዙር ጥሪ አቅርቧል፡፡
በመሆኑም መገናኛ ብዙኃን የማመልከቻ ቅጹን እና አስፈላጊ ሠነዶችን በቦርዱ ማህበራዊ ተስስረ ገፅ የተቀመጡ ማስፈንጠሪያዎች በመጠቀም ከቦርዱ ድረ-ገጽ በማውረድ ወይም ፊላሚንጎ ሬስቶራንት ገባ ብሎ በሚገኘው የቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት ቢሮ ቁጥር 308 መውሰድ እንደሚችሉ ገልጿል ፡፡
ተቋማቱ ሞልተው የተጠናቀቁትን ማመልከቻዎቻቸውን ይህ ማስታወቂያ ከወጣበት ከሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 5 ቀናት በኢ-ሜል አድራሻ media@nebe.org.et በመላክ ወይም ዋናው መሥሪያ ቤት በአካል በመገኘት ማስገባት እንደሚቻል በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባወጣው መረጃ አስፍሯል።