AMN-ግንቦት 05/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽ እና በጋራ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሰፋ ያለ ውይይትም አካሂደዋል።
በውይይቱ ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸው ቁልፍ ስምምነቶችን ያካሄዱ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የታዳሽ፣ የተቀናጀ እና ዘላቂ ኃይልን ለማስፋፋት እንዲሁም የዲጂታላይዜሽን ፕሮግራምን ለመተግበር የሚውል የ54.6 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በተጨማሪም የ150 ሜጋ ዋት የጂኦተርማል (የእንፋሎት) ኃይል ልማትን በመንግሥትና በግል አጋርነት ለመተግበር የሚያስችል አዲስ የማዕቀፍ እና የፍኖተ ካርታ ልውውጥ ተደርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት “ተሻጋሪ ርዕይን የሰነቀ አጋርነት” መሆኑን ገልጸው፤ ጉዞው ወደ ብሩህ መጻኢ መሆኑን አመልክተዋል።
መሪዎቹ በቆይታቸው በሳይንስ ሙዚየም ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ ይህም ለሁለቱ ሀገራት መጪው ዘመን ለላቀ ፈጠራ፣ ለቴክኖሎጂ ዕድገት እና ከፊት ለፊት ለሚታዩ ሰፊ ዕድሎች ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ የፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጉብኝት በኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ መካከል ያለውን የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ ትብብር የሚያሸጋግር መሆኑ ታምኖበታል።
በሚካኤል ህሩይ